ከሲዳማ ቡና ኣምራቾች ጋር በመስራቷ የምትታወቀው ጃፓን በኣጠቃላይ በኣገሩ የቡና ምርት ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ካነሳች ከስድስት ዓመት በኋላ በቡና ጥራት አለመደሰቷን ይፋ አደረገች

ወሬው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው
ፎቶ ከኢንተርኔት ላይ
ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ጃፓን በተላከ የቡና ጆንያ ላይ በተገኘ የኬሚካል ቅሪት ሳቢያ ጃፓን ከኢትዮጵያ የሚላከውን ቡና አግዳ ብትቆይም፣ አሁንም በሚላክላት ቡና ላይ የጥራት ጉድለት እየታየ በመሆኑ የቀድሞውን ያህል እየገዛች አለመሆኗ ተገለጸ፡፡ 
በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ከስድስት ዓመት በፊት በፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ሳቢያ ጃፓን ትገዛው የነበረው ቡና ለተወሰነ ጊዜ ከተቋረጠ በኋላ መልሶ ማገገም ቢጀምርም፣ ከስድስት ዓመት በፊት ወደነበረበት ደረጃ ሊመለስ አልቻለም ብለዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ጥራት ያለውና ከፍተኛ ደረጃ የተሰጠው ቡና ተብሎ የሚላከው ጥራቱም ደረጃውም ዝቅተኛ ከሆነው ጋር እየተደባለቀ በመገኘቱ እንደሆነ አምባሳደር ሱዙኪ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የሚፈለገውን ያህል ቡና ወደ ጃፓን መላክ ባይቻልም በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ግን ተነግሯል፡፡ 
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በዓመት ከ170 እስከ 190 ሺሕ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ ይቀርባል፡፡ ከዚህ መጠን ውስጥ የጃፓን ድርሻ ግን ከአሥር በመቶ እንደማይበልጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአንፃሩ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ጃፓን ይላክ የነበረው የቡና መጠን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት እስከ 25 ከመቶ ይደርስ ነበር፡፡ 
የኬሚካል ንክኪውን ለማስቀረት የጃፓን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በጃፓን መንግሥት ድጋፍ የላቦራቶሪ ማዕከል ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ከመደበኛው ቡና ጋር ተቀላቅሎ እየተላከ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቡና የጃፓንን የጥራት ደረጃዎች ማሟላት ተስኖት እንደሚገኝ አምባሳደሩ ይናገራሉ፡፡ ይህ ቢስተካከል ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ጥራት ያላቸው ልዩ ቡናዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አምባሳደር ሱዙኪ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥሬ ቡና ባሻገር አገር ውስጥ የተቀነባበረ ቡና የመላክ ሐሳብ እንዳላት ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ይህንን ለማድረግ ግን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪው መዳበር እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር