በበጀት አመቱ በዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ በብዛት ከተላኩት ሲዳማ ቡና 32.1% በመያዝ ትልቁን ድርሻ ይዟል
በዘጠኝ ወሩ ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ፣የቅመማቅመምና የሻይ ቅጠል ምርቶች 560 ሚሊየን ዶላር ማግኘት ተችሏል
በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት ከቡና ፣ከቅመማ ቅመምና ከሻይ ቅጠል ምርቶች 148 ሺ 227 ነጥብ 2 ቶን ተልኮ 560 ሚሊየን ዶላር ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳኒሶ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለስልጣኑ 17 ሺ 354 ነጥብ 72 ቶን በመላክ 649 ሚሊየን ዶላር ለማግኝት አቅዶ ነበር፡፡
ባለስልጣኑ ካቀደው በመጠን 85.55 በመቶው ከገቢ ደግሞ 86.3 በመቶውን ማሳካት ችሏል፡፡
አፈጻጸሙ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 4.5% በገቢ 15% ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል፡፡
ወደ ውጭ ከተላከ 139 ሺ 887 ቶን የቡና ምርት ብቻ 545 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ የእቅዱን በመጠን 88.12 % ና በገቢ 87.91 % መሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በበጀት አመቱ በዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ በብዛት ከተላኩት ሲዳማ ቡና 32.1% በመያዝ ትልቁን ድርሻ ሲይዝ በመቀጠል የነቀምት ፣፣ የጅማ፣ የሀረር፣ የይርጋ ጨፌና እና የሊሙ ቡና በየደረጃቸው መላካቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሀገራት 59 ሲሆኑ ሳውዳረቢያ 17.72 % ጀርመን 17.41፣ ጃፓን 10.25፣ ቤልጂየም 8.44%ና አሜሪካ 7.62% በመያዝ ቀዳሚውን ቦታ የያዙ እንደነበርም ታዉቋል፡፡
ዘንድሮ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ምርት የተገኘበት ሲሆን ለገበያ የቀረበውም በተመሳሳይ የተሻለ ነው ተብሏል ፡፡
የዘጠኝ ወሩን እቅድ ለምን መቶ በመቶ ማሳካት አልተቻለም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በአንደኛና በሁለተኛ ሩብ አመት ለገበያ የሚቀርበው የባለፈው አመት ምርት በመሆኑና በሚፈለገው መጠንም ማግኘት ባለመቻሉ ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ 241 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 941 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር አቅዶ እየሰራ መሆኑም ታውቋል፡፡
በቀሪዎቹ ሶስት ወራት የቡና ምርት ለገበያ የተሻለ የሚቀርብበት በመሆኑ የአመቱን እቅድ ለማሳካት እንደሚቻልም ተመላክቷል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜኣ
Comments
Post a Comment