የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከቦንድ ግዥ በተጨማሪ በምርምር ስራ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡
የህዳሴ ግድቡን ዋንጫ አቀባበል ምክንያት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች ለግድቡ ግንባታ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቶ አያኖ በራሶ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል ገብቷል፡፡
የህዳሴ ግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በቦንድ ግዥ፣ በዕውቀትና በክልሉ በግድቡ ዙሪያ በሚደረጉ የውይይት መድረኮች የተቋሙ ምሁራን ሙያዊ ማብራሪያ በመስጠት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በምርምር ረገድም ራሱን የቻለ የውሀ ዘርፍ እንዳለው ጠቁመው በቀጣይም የአባይ ውሀ ሀገሪቱ የበለጠ መጠቀም የምትችልበትን ሁኔታን በጥናት በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አቶ አያኖ ገልጸዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ ሀዋሳ መግባቱን ተከትሎ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች በስጦታና በቦንድ ግዥ ከ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡
በግላቸው ለሶስተኛ ጊዜ በወር ደመወዛቸው የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የኬሚስትሪ የትምህርት መስክ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዮርዳኖስ ገብረስላሴ በበኩሏ የአባይ ወንዝ ለሀገሩ ጥቅም እንዲሰጥ የግድቡ መገንባት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሳ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ወደ ዩኒቨርሲቲው መምጣቱ እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡
የኮምፒውተር ሳይንስ የአራተኛ ዓመት ተማሪው  ታደሰ አይጠገብ በሰጠው አስተያየት ከኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች አንዱ የሆነው አባይ ተገድቦ ጥቅም ላይ መዋሉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት እንደሚያስችል ገልጿል፡፡
የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን የተነሳ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ላይ እየተስተዋለ ያለውን የመቆራረጥ ችግር ማስቀረት ያስችላል ነው ያለው ተማሪ ታደሰ፡
 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር